በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የዳዉሮ ተርጫ ካምፓስ ተመረቀ
ለወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ሶስተኛ ካምፓስ የሆነዉ የዳዉሮ ተርጫ ካምፓስ የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣የሚኒስቴር መስሪቤቱ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣የደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች የክልል የተለያዩ አመራሮች፣የወላታ እና ዳዉሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪዎችና ሌሎች አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተመርቋል፡፡
በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ መንግስት የህብረተሰባችንን የልማት ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ መልኩ ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ በፍታሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ትምህርት፣ምርምር እና ሳይንሳዊ ባህሎችን እያጎለበትን መሄድ ሀገራችን ለምታደርገዉ የዕድገትና የብልጽግና ጉዞ የማይተካ ሚና ስላላቸዉ ዩኒቨርስቲዎቻችን ይህንኑ በዉል በመገንዘብ በትጋት መተግበር እንዳለባቸዉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ለፍትሐዊነትና ተደራሽነት የትምህርት ተቋማትን በምናስፋፋበት ወቅት ተቋሞቻችን ለትምህርት ጥራትም ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡
የዳዉሮ ዞን ዋና ከተማ የሆነችዉ ተርጫ ከተማ ከወላይታ ሶዶ 170 ኪ.ሜ በላይ ርቃ የምትገኝ ስትሆን በዚህ ርቀት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በዳዉሮ ዞን ተጨማሪ ካምፓስ መክፈቱ የሁለቱን ዞኖች ህዝቦች በጋራ የመልማት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለዉ የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ሌሎች አከባቢዎችም ከዚህ መማር አለባቸዉ ብለዋል፡፡