News

የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ሀምሌ 5/2013 ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛ

Posted 2021-07-14
Card image

የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ሀምሌ 5/2013 ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛ


የዝግጅቱ መክፈቻ በኢቢሲ ዜና ቻናል እና በሚኒስቴር መ/ቤቱ የፌስቡክ ገጽ በቀጥታ እየተላለፈ ሲሆን የቀጥታ ስርጭቱን ላልተከታተላችሁ ያለፉት ሁለት ቀናት ዉሎ እንደሚከተለዉ ቀርቧል፡፡


=====================================


በመጀመሪያ ቀን ዉሎዉ….


#አገራዊ የልማት ዕቅዶቻችን እንዲሳኩ የሳይንስ የቴክኖሎጂ የፈጠራ እና የሰው ሃብት ልማት ስራዎቻችን ማጠናከር እንደሚገባ ተገጸዋል፡፡

መድረኩ “ወደ እውቀት መር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን ዓላማውም የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ማበረታታት፣ እዉቅና መስጠት እና ትስስርን ማጠናከር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ 

ክብርት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ለሀገራዊ የልማትና ብልፅግና ግቦቻችን ስኬት ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት፣ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን በጥናትና በምርምር በማፍለቅ እና ተደራሽበ ማድረግ፣ አግባብነት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች ለኢንዱስትሪ እና አገልግሎት በማሸጋገር እንዲሁም በእውቀት ላይ የተመሰረተ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ተቋማዊ የትስስር ስራዎችን በመምራት ተግባርና ሃላፊነቱን በጥራት፣ በስፋትና በፍጥነት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች የተማርናቸው እና ያሻገሩን የሀገር በቀል እውቀቶች እና ሳይንሳዊ መፍትሔዎች እንዲዳብሩ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ብርቱ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እና ፕሮግራሞችን ቀርፀው ለትግበራ በቅንጅት መረባረባቸዉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቷ። 

ለዚህም ሳይንስ ተኮር በመሆን ውጤት ላይ ያተኮረ የምርምር ባሕል ማስፈን፤ ለፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ልዩ ትኩረት መስጠት፤ ሥራ ወዳድና ፍሬያማ የሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ዜጋን ማፍራት፤ በተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የእቅድና የተግባር መጣመርና መተሳሰርን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ክቡር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ መንግስት የቀጣይ 10 ዓመት የልማት ዕቅድ መዳረሻው ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማሳካት ሲሆን ይህንን ዕቅድ ለማሳካት በተለመደው የአሰራር ስርዓት፣ ሳይንሳዊ እውቀትን የማመንጨትና የመጠቀም፣ የሰው ሀይል ልማትና ዕድገት እንዲሁም የስራ ዕድል የመፍጠር ባህልን ይዘን ማሳካት አይቻልም፡፡

በመሆኑም ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሳይንሳዊ ግኝቶችንና የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ ለሀገራቸውና ለዓለም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ተቋማዊና ዘላቂነት ያለው አሰራር ማበጀት በማስፈለጉ ይህ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና መሰል ዘርፎች ዕውቀትን፣ ክህሎትን እና ጥበብን የእድገት ማጎልበቻና አጋዥ መሳሪያ አድርገን ለመጠቀም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው የኮንቬንሽኑ ትኩረት የትምህርትና የምርምር ተቋማት ለሀገራዊ ልማት ግቦች ስኬታማነት የሚኖራቸውን ሚና ማጠናከር መሆኑን ጠቅሰው የዕውቀት መር ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደት በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል መኖር፣ ዕውቀት ማመነጅጨትና መጠቀም እንዲሁም ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ መሰረት ያደርጋል፡፡  

በመድረኩ ሦስት የሽልማት አይነቶች የሚሰጡ ሲሆን የመጀመሪያውና ትልቁ የኢትዮጵያ የሳይንስ ሽልማት ነው፡፡ ሁለተኛው አገራዊ የልህቀት ሽልማት እንዲሁም የመጨረሻው ብሔራዊ የምስጋና ሽልማት ሲሆን የመጀመሪያው ሽልማት በዚህ ዓመት የማይሰጥ እንደሆነ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡


======================================

ሀምሌ 6/13 ሁለተኛዉ ቀን ዉሎ .......


 ’ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ለዘላቂ እድገት በዓለም ፣ በአህጉር እና በአገር አቀፍ ደረጃ’ በሚል ጭብጥ የተለያዩ አምስት ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

’ያደገች ኢትዮጵያን ለማየት በተለዩ የልማት ዘርፎች አብዮት ያስፈልጋል፡፡’’

   ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ;-የትምህርት ሚንስትር


=====================================


በተለያዩ የግልና የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምርምርና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ለአውደ ርዕይ ተከፍተው ጉብኝት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት የአገሪቱን ችግር በእውቀት መር ኢኮኖሚ ለመምራት የሚያስችሉ ከፍ ያሉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡

በጉባኤው ’ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ለዘላቂ እድገት በዓለም ፣ በአህጉር እና በአገር አቀፍ ደረጃ’ በሚል ጭብጥ የተለያዩ አምስት ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

በጉባኤው የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ዓለም አሁን ለደረስችበት የእድገት ደረጃ ያለፈችባቸውን ጎዳናዎች አውስተው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የጀመረው የእንዲስትሪ አብዮት ሰዎች የሰውና የእንስሳት ጉልበት መጠቀምን አቁመው ፊታቸውን ወደ ኢንዱስትሪ እንዲያዞሩ አድርጓል ብለዋል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የሰውና የእንስሳት ጉልበት እየተጠቀመች እድገት ለማምጣት እየታተረች ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ይህንን በማስቀረት ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት አገራዊ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ የተቀረጸ ሲሆን ያደገች ኢትዮጵያን ለማየት በግብርና፣ በማንፋክቸሪንግና በትራንስፖርት ዘርፎች አብዮት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዓለም ያደጉና በፍጥነት እያደጉ ያሉ ኢኮኖሚዎችን ለአብነት ያነሱት ሚንስትሩ እድገት በትራንፎርሜሽን ሳይሆን በአብዮት እንደመጣ ያሳያል ብለዋል፡፡

በዚህም ለኢትዮጵያ እድገት ’የንግድ ሚዛን’ ሳይሆን ’የቴክኖሎጂ ሚዛን’ መጠበቅ የግድ ያስፈልጋል፡፡

በከፍተኛ ምሁራንና አገር መሪዎች ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው ፓናል ከሰዓት በኋላ ዉሎዉ በዲፕሎማሲና ውጭ ግንኑነት ላይ ተወያይቷል፡፡


====================================


በሁለተኛዉ ቀን ዉሎ በሌላኛዉ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፤-  


የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ሀምሌ 5/2013 ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ሀምሌ 06/11/13 ሁለተኛዉ ቀን ዉሎ በሁለት ዋና ዋና ርዕሰጉዳዮች ላይ በሁለት አዳራሾች ፓናሎች ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 16 ጆርናሎች እውቅና ተሰቷቸዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ ሳይንሳዊ ጆርናሎችን እውቅና በመስጠት እንዲታተሙ የምታደርገው በአህጉራችን ደቡብ አፍሪካ ብቻ ናት፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያም ስርዓቱ እንዲዘረጋ ተደርጎ የመጀመሪያው ዕውቅና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

የምርምር ተቋማትና የሳይንሳዊ ህትመቶች አርታኢያን የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ማደራጀት፣ መተንተንና ማሰራጨት ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከሁሉም በላይ ጥራት ማስጠበቁ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገ/ማርያም በበኩላቸው አካዳሚው ለሳይንሳዊ ህትመቶቹ መለያ ዝርዝር መስፈርቶችን አውጥቶ ለሁሉም ክፍት አድርጓል፡፡ በዚህ መሰረት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በኩል 30 የሚደርሱ ህትመቶች መቅረባቸዉን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩም የተቀመጠዉን መስፈርት ላሟሉ 16 ጆርናሎች የእውቅና ሰርተፊኬት የተበረከተ ሲሆን የፓናል ዉይይትም ተካሄዷል፡፡


=====================================


በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናው ዘርፍ ላይ የሚያተኩር ውይይትም ተካሂዷል፡፡


"በዘርፉ አውቆ፣ ልቆና ትጽእኖ ፈጥሮ የሚመራ አመራር ያስፈልጋል" አቶ ንጉሱ ጥላሁን :- የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር


በመድረኩ ሀጉራዊ የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ለዕድገት ያለው አስተዋጽኦ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ለስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ዞኒንግ ለተቀናጀ ዘላቂ ልማት ያለው ፋይዳ ላይ ያተኮሩ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በሀገራችን መተግበር ከጀመረበት አንስቶ በርካታ መልካም ስራዎች ተሰርተዋል፤ ሰፊ የስራ ዕድልም መፍጠር ተችሏል፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ በስራ ገበያው የሰው ሃይል ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ይስተዋላል፡፡

ይህም በአንድ በኩል ኢንዱስትሪው እጁ የተፍታታ እና መስራት የሚችል የሰው ሃይል የሚፈልግ ሲሆን በሌላ በኩል የትምህርትና ሥልጠና ተቋሞቻችን ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት አልቻሉም፡፡ ይህም በፍጥነት ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የፌዴራል መንግስት የሚኖረው ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ የክልሎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በየደረጃው የሚገኘው የዘርፉ አመራር ዘርፉን አውቆ፣ ልቆና ለሌሎች እያስረዳ ተጽዕኖ ፈጥሮ የሚመራ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ በበኩላቸው፣ ዘርፉ ለአገራዊ ዕድገታችን ካለው ፋይዳ አኳያ ዘርፉን የሚመሩ አመራሮች ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው በኢትዮጵያ ለሙያተኞች ዝቅተኛው መነሻ ክፍያ ትኩረት ተሰጥቶት ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡

Pictures


News

Card image
2021-07-09
Registration Criteria for Individual Researchers
Card image
2021-05-25
2012 E.C Top 100 Students Based on Entrance(Grade 12) Exam Result
Card image
2021-05-25
2012 E.C Top 100 Female Students Based on Entrance(Grade 12) Exam Result
Card image
2021-05-08
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር የተፈታኞች ቅሬታ ማቅረቢያ ቅጽ 2013 ዓ.ም
Card image
2021-04-30
H.E. Dr. Samuel Urkato visited Misale Driver training academy
Card image
2021-04-14
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ፕሮግራሞች ዝርዝር